ወደ ዋና ይዘት ዘለው ይሂዱ

ያላለቀ ድርሰት


ያላለቀ ድርሰት

Written by  አንተነህ ይግዛው

     “ኧረ ይብቃህ ደጀኔ!... አራት ሰዓት ሞላኮ!...” አሉ እትየ ስንዱ፣ መጋረጃውን ገለጥ አድርገው ከወደ ጓዳ ብቅ እያሉ፡፡ “አንቺ ግን ለምን ሰላም አትሰጪኝም!?...” ደጀኔ አቀርቅሮ ከሚጽፍበት ቀና በማለት በንዴት ጦፎ እስክርቢቶውን ወረወረ፡፡ “ስንቴ ልንገርሽ አክስቴ!?… በውስጤ የታመቀውን የደራሲነት ስሜት መተንፈስ እንጂ፣ የኮሌጅ ትምህርት አጠናቆ መመረቅ አይደለም የህይወቴ ጥሪ!” እየተንቀጠቀጠ ተናገረ፡፡ “የዛሬውስ የተለየ ነው!... ገና በማለዳ ንትርክ ጀመራችሁ?” የእማማ በለጡ ድምጽ በስተቀኝ ያለውን የኮምፔርሳቶ ግድግዳ አልፎ ተሰማ፡፡ ከጉዳይ የጣፋቸው አልነበረም፡፡ “ተው እንጂ ደጀኔ… ደህና ሂደህ ሂደህ አንድ አመት ሲቀርህ አትሰላች!” በትህትና መለሱለት፡፡ “አንቺኮ ችግርሽ ይሄ ነው!... የጀመርኩትን ትምህርት እንጂ፣ የጀመርኩትን ድርሰት ስለመጨረሴ አትጨነቂም!” ከተቀመጠበት ብድግ አለ፡፡ ሁለት አንቀጽ ጅምር አጭር ልቦለድ የጻፈባትን ወረቀት ከጠረጴዛው አንስቶ በፍጥነት ወደ ጓዳ አመራ፡፡
“እኔኮ ላንተ ብየ ነው!... ደሞም’ኮ አትጣፍ አላልኩህም፡፡ ከኮሌጅ ስትመለስ መጨረስ ትችላለህ” አሉት አክስቱ በትህትና ፈገግ ብለው፡፡ የአክስቱ ትህትና የገነፈለ ስሜቱን በረድ አደረገለት፡፡ እንደወትሮው አልተቆጡትም፡፡ እንደሌላው ጊዜ ልብ የሚሰብር ነገር አልተናገሩትም፡፡ “ደሞ አንተን ብሎ ደራሲ!... የአስር ሳንቲም ሻይ ቅጠል የማይገዛ እንቶፈንቶ መሞንጨሩን ትተህ፣ ትምህርትህን ብታጠና ይሻልሃል!” ብለው አልተሳለቁበትም፡፡ ወደ ጓዳ የጀመረውን ጉዞ ገታ አደረገና ዘወር ብሎ ተመለከታቸው፡፡ አክስቱ ፊት ላይ ባዕድ ፈገግታ ተመለከተ፡፡ ጥቂት አሰብ አደረገና በእጁ የያዘውን ወረቀት በተስፋ መቁረጥ ወደ ጓዳ ወረወረው፡፡ “ማንም ተጠያቂ አይደለም…” ብሎ ጀምሮ፣ ሁለት አንቀጽ ከተጓዘ በኋላ ሳይቋጭ የቀረው የደጀኔ ጅምር አጭር ልቦለድ፣ እየተውለበለበ ወርዶ ጓዳ የተቀመጠ መክተፊያ ላይ አረፈ፡፡ ደጀኔ ከአክስቱ ቤት ወጥቶ ወደ ኮሌጅ ሄደ፡፡
ደጀኔ ከኮሌጅ ወጥቶ ወደ አክስቱ ቤት ተመለሰ፡፡ ከላይ ባሉት ሁለት አረፍተነገሮች መካከል ብዙ ነገር ተከናውኗል፡፡ “ስንዴ ቡናው ፈልቷል” ብለዋል እማማ በለጡ፡፡ ደጋግመው ተጣርተዋል… ምላሽ አጥተዋል፡፡ ወደ እትየ ስንዱ ቤት መጥተዋል፡፡ “የት ገባች ይቺ ሴትዮ?” ጠይቀዋል - ስንዱን ከሳሎን ሲያጡ፣ ወደ ጓዳ እያዩ መጋረጃውን እየገለጡ፡፡ “እሪሪሪሪሪ!!!!!” ብለዋል በፍርሃትና በድንጋጤ እየተንቀጠቀጡ፣ መንደሩን በጩኸት እያቀለጡ፡፡ እትዬ ስንዱ ተፈጽመዋል፡፡ በእንስራ ገመድ ራሳቸውን አንጠልጥለዋል፡፡ መንደርተኛው በለቅሶ ሲናወጥ፣ ዙሪያ ገባው በዋይታ ሲቀወጥ፣ ልጅ አዋቂው በእንባ ሲራጭ… ይህ ሁሉ ሲሆን ከቆየ በኋላ ነው፣ ደጀኔ ከኮሌጅ ወደ መንደሩ የተመለሰው፡፡ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ - ደጀኔ የሆነውን ሁሉ ሲሰማ፡፡ “አክስቴን… ስንዱዪን!... ምነው ምን አረግኩሽ!?... ለማን ትተሽኝ ሄድሽ?... እኔ ልሰቀልልሽ!...” እያለ መሬት ላይ ወድቆ ተንከባለለ፡፡ ጎረቤት ተባብሮ ከመሬት ሲያነሳው ደግሞ፣ ለመሮጥ ሞከረ፡፡ ወዴት?... ወደ እማማ በለጡ ውሃ ጉድጓድ!... ለምን?... ራሱን ለማጥፋት! “የኔ ጉድጓድ የማንም እርኩስ መደበቂያ ነው እንዴ?!” አሉ እማማ በለጡ ነገሩን ሲሰሙ፡፡ ደጀኔ ሴትዮዋ “መደበቂያ” የሚለውን ቃል ያለነገር እንዳልተጠቀሙት የገባው ዘግይቶ ነው። ጎረቤቶቹ አረጋግተው ካስቀመጡትና የሆነውን ሁሉ ከነገሩት በኋላ ነው ነገሩ የተገለጠለት፡፡
ፖሊስ ነገሩን ሊያጣራ መጥቶ እንደነበርና መረጃ ሰብስቦ እንደሄደ ከጎረቤት ሰማ፡፡ እማማ በለጡ ፖሊሶች ከሄዱ በኋላ የእሱን ስም እየጠሩ አጉል ነገር ሲናገሩ እንደነበር ተነገረው፡፡ “ጧት ስንዱና ደጀኔ ሲጨቃጨቁ ሰምቻለሁ፡፡ እሱ ከሄደ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ቡና ጠጪ ልላት ስሄድ ተንጠልጥላ አገኘኋት፡፡ እሱ ነው አበሳጭቶ ያለጊዜዋ የደፋት” ሲሉ ነበር አሉት፡፡ ስለዚህ ደጀኔ በአክስቱ ሞት ተጠርጣሪ ነው። ለምርመራ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ከተወሰደው አስከሬን ጋር የሄደች አንዲት ሴት “ፖሊሶቹ ስንዱ ከመሞቷ በፊት የጻፈችውን ኑዛዜ አግኝተዋል” የሚል አዲስ መረጃ ይዛ መጣች፡፡ ይህ ነገር ብዙዎችን አስደነቀ፡፡ ‘እሱ ነው አቃጥሎ የገደላት’ ብለው፣ ደጀኔን ውስጥ ውስጡን ሲያሙ የነበሩ ሁሉ ተገረሙ፡፡ ደጀኔም ቢሆን ወሬውን ሲሰማ ግራ መጋባቱ አልቀረም። አክስቱ መጻፍ እንደሚችሉ አያውቅም ነበር። ይሄም ሆኖ ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርገው የአክስቱ ኑዛዜ በመገኘቱ ተጽናና፡፡
በዚህ መሃል ነው መርማሪው ፖሊስ ከተፍ ያለውና ከደጀኔና ከቅርብ ሰዎች ጋር መወያየት የጀመረው፡፡ ተገኘ የተባለው ጽሁፍ በሌላ ሰው ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ አለመሆኑንና እርግጥ ሟቿ የጻፉት እንደሆነ ለማረጋገጥ፣ ሌላ ከዚህ በፊት የጻፉት ጽሁፍ ካለ እንዲቀርብለት አዘዘ ፖሊሱ፡፡ ያልተበረበረ ቁምሳጥንና ሻንጣ የለም፡፡ ደጀኔ ወደ ጓዳ ገብቶ የአክስቱን የእጅ ጽሁፍ መፈለግ ጀመረ፡፡ የአክስቱ የእጅ ጽሁፍ ጓዳ የለም። የአክስቱ ብቻ ሳይሆን የእሱም የእጅ ጽሁፍ የለም፡፡ “ማንም ተጠያቂ አይደለም…” ብሎ ጀምሮ፣ ሁለት አንቀጽ ከተጓዘ በኋላ ሳይቋጭ የቀረው ጅምር አጭር ልቦለዱ፣ ጧት ላይ ተናዶ ወደ ጓዳ የወረወረው የእጅ ጽሁፉ! ደጀኔ ነገሩ ተገለጠለት፡፡ የለቀስተኛ ድምጽ እየረበሸው፣ ጓዳ ተደብቆ የሆነ ነገር ለመጻፍ ሞከረ… የሆነ ነገር… በቃ… አለ አይደል… ለፖሊሶቹ የሚሆን… ከጓዳ ያገኙትን የአክስቱን ኑዛዜ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚረዳ የአክስቱ የእጅ ጽሁፍ…

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ያማል! ገጣሚ ሰለሞን ሳህለ

እንደነገርኩሽ… የሚወዱትን ሰው - ቀጥሮ እንደመጠበቅ፣ የነፍሰ ጡርን ሞት - አይቶ እንደመሳቀቅ፣ ባልታሰበ ናዳ - ተመትቶ እንደመድቀቅ፣ ከተስፋ ጉልላት - ተገፍቶ እንደመውደቅ፣ ታምር በበዛባት - በዚህች ቧልተኛ ዓለም፣ ከዚህ የበለጠ - ምንም ህመም የለም፡፡ አውቶብሱ ያማል፣ ሚኒባሱ ያማል፣ ላዳ ታክሲው ያማል፣ የማይጎል የሰው ጎርፍ ደራሽ ማዕበሉ፣ የእንባ ቅጥልጥሉ፣ ምን ብዬ ልንገርሽ - ያማል ይሄ ሁሉ፡፡ እና እንደነገርኩሽ… የሚወዱትን ሰው ቀጥረው ካረፈደ፣ የሚያፈቅሩትን ሰው ቀጥረው ካረፈደ፣ ነገር ተበላሸ - ህመም ተወለደ፡፡ ጨጓራ በገነ፣ እሳት በእንፋሎት መልክ በእህታ ተነነ፡፡ የሚሆነው ሳይሆን የማይሆነው ሆነ፡፡ ሁሉም ተቀይሮ ተተካ በሲቃ፣ ምን ብዬ ልንገርሽ ይህም ያማል በቃ፡፡ ወጪ ተራማጁ፣ አስመሳይ ሰጋጁ፣ ፀሐዩ ዝናቡ፣ የለምን ምክንያት የለምን ሰበቡ፣ ተቆራጭ አበባ ሊቆረጥ ማበቡ፣ ውል የለሽ ደመና ተራራ መክበቡ፣ እልፍ አዕላፍ ኮከብ ጨረቃን ማጀቡ፣ ደግሞ ለእሷ ግጥም እናቷን ጨረቃ፣ ምን ብዬ ልንገርሽ ይህም ያማል በቃ፡፡ እና እንደነገርኩሽ… ጉንጭ የማትሞላ ኬክ 10 ብር የሸጠ፣ የካፌ አሳላፊ ወደ እኔ አፈጠጠ፡፡ ዘይት የነካውን መንታ እጁን አጣምሮ፣ ምን ልታዘዝ ይላል ቁልቁል አቀርቅሮ፡፡ ምን ልታዘዝ ይላል… እንዴት ቅጥሉ ሰው ቅጥሉን ሰው ያዛል፣ ማኪያቶ ልዘዝ…? ካፑቺኖ ልዘዝ…? ጥቁ ቡና ልዘዝ…? ለምን ሰው አላዝም… መታዘዝ መናዘዝ ርግማን የሆነው፣ ካፌውን ሲያሳልፍ፣ ራሱ ግን የሚያልፍ፡፡ ቁልቁል አቀርቅሮ፣ ሞቱን ባንገት ቀብሮ፣ ምን ልታዘዝ ይላል… አንድ ማኪያቶ - ካንድ እሷ ጋር ልበል… አንድ ካፑችኖ - ካንድ እሷ ጋር ልበል… ከጥቁር ቡና ጋር - እሷን ...
ከጥቁር ሰማይ ስር በእንዳለጌታ ከበደ ጥዋት ጥዋት፣ ወደ ቢሮ ለመሄድ - መታጠፊያው ጋ ሲደርስ - እተለመደ ቦታዋ ቁጭ ብላ የሚያጉተመትም በሚመስል ድምጿ ያለማቋረጥ ስታወራ ይሰማታል፡፡ የአራት ልጆች እናት የሆነችዋን የኔ ቢጤ፡፡ የእናታቸውን ያህል ባይሆንም ጎስቁለዋል፡፡ እንደ ምጣድ ማሰሻ የቀድሞ ከለሩ ያልታወቀ ከነቴራ ለብሰዋል - ከወገባቸው በላይ፡፡ ከመሃከላቸው አንዳቸውም ቃጭል አንጠልጥለው አልተወለዱም፡፡ . . . በማያውቀው ቋንቋ ታወራቸዋለች፡፡ ልጆቿ አይመልሱላትም፡፡ እርስ በርሳቸው ሲጨዋወቱ በአዲስ አበባ አማርኛ ነው የሚግባቡት፡፡ እንዲህ በከንቱ ጉንጭዋን የምታለፋው በውስጡ ያደረውን ጩዋሂ መንፈስ ላለማዳመጥ ይሆን? ብሎ ያስባል ጤንነቷን የማይጠራጠር የለም፡፡ አንዳንዶች ፥ ስለ ልጆቿ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማሰላሰል ስታበዛ ይሆን ያተሳሰብ ማዛንዋ የተዛባው? ይላሉ፡፡ ሁልጊዜ ያልተለመደ ነገር ስታደርግ ያጋጥመዋል፡፡ እጇ ላይ የተገኘን ማንኛውም ነገር ለአራት አካፋፍላ ለልጆች ታድላቸዋለች፡፡ ለራሷ የምታደርገው አይኖራትም፡፡ ከሲታ ናት ደግሞ፤ ያለ እህል ውሃ ለመኖር ሙከራ የጀመረች እስኪመስል ድረስ፡፡ ሳንቲም ተወርውሮ እግሯ ስር ያረፈ እንደሆነ ቅጭልጭልታውን ሰምታ እንኳን ቀና አትልም፡፡ ማንንም አይታይም - አገጯን ጉልበቷ ስር ደብቃ ነው፤ ቀኑን ውላ የምታመሸው፤ የምታነጋውም! መንገድ ዳር፡፡ እሷ ካለችበት ፈንጠር ብሎ - አንድ ክፉ የማይመስል - ዘባተሎ ለባሽ ጎልማሳ - በጠባቂነት መንፈስ ዓይኑን ያንከራትትባቸዋል፡፡ በየመንገዱ የሰበሰባቸው ቁርጥራጭ ሲጋራዎች ከኪሱ እያወጣ ያጨሳል፡፡ የልጆቿ አባት ይሆን? . . . ወይስ ወደ ጎዳና ከወጣች በኋላ የተወዳጃት ጊዜያዊ ባል?! . ...